በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃይማኖት መነገጃ እየሆነ ነው?

ሃይማኖት መነገጃ እየሆነ ነው?

 ብዙ ሃይማኖቶች መንፈሳዊ ትምህርት ከመስጠት ይልቅ ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ እያተኮሩ እንደመጡ አስተውለሃል? የተለያዩ አገልግሎቶችንና ምርቶችን ያስተዋውቃሉ እንዲሁም ይሸጣሉ። ብዙ የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ደሞዝ ይከፈላቸዋል፤ የቅንጦት ሕይወትም ይመራሉ። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  •   በአንድ ምርመራ እንደተደረሰበት አንድ የካቶሊክ ጳጳስ በ13 ዓመት ጊዜ ውስጥ 150 ጊዜ ገደማ በግል አውሮፕላን ለመጓዝ እንዲሁም 200 ጊዜ ገደማ በሊሞዚን ለመጓዝ የቤተ ክርስቲያኑን ገንዘብ ተጠቅሟል። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚገኘውን መኖሪያውን ለማደስ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል።

  •   በአንድ የአፍሪካ አገር የአንድን ሰባኪ ስብከት ለማዳመጥ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሰበሰባሉ። ግዙፍ በሆነው የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ውስጥ የማይሸጥ ነገር የለም ማለት ይቻላል፤ ለምሳሌ የተጸለየበት ዘይት እንዲሁም የሰባኪውን ምስል የያዙ ፎጣዎችና ቲሸርቶች ይሸጣሉ። እዚያ ከሚሰበሰቡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ድሆች ቢሆኑም እሱ ግን የናጠጠ ሀብታም ሆኗል።

  •   ቻይና ውስጥ በቡድሂዝም እምነት ቅዱስ ተደርገው ከሚቆጠሩት አራት ተራሮች መካከል ሁለቱ በንግድ ኩባንያ ስም እንዲመዘገቡ ተደርጓል። ታዋቂው የሻውሊን ቤተ መቅደስም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይሳተፋል፤ የቤተ መቅደሱ የመነኮሳት አለቃም በስፋት የሚታወቀው ዋና ሥራ አስኪያጁ መነኩሴ በሚለው መጠሪያ ነው።

  •   በመላው አሜሪካ የሚገኙ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች መንፈሳዊ አማካሪዎችን መቅጠር ጀምረዋል። አንድ ሪፖርት እንደገለጸው እነዚህ አማካሪዎች የተለያዩ ሃይማኖቶችን ሥርዓቶች በመኮረጅ የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይቀርጻሉ። እንዲሁም ለደንበኞቻቸው ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ።

 በንግድ ሥራ ስለተጠላለፉ ሃይማኖቶች ስታስብ ምን ይሰማሃል? በሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ስም ትርፍ ለማጋበስ ስለሚሞክሩ ሰዎች አምላክ ምን እንደሚሰማው አስበህ ታውቃለህ?

አምላክ ሃይማኖትን ከንግድ ጋር ስለመቀላቀል ምን ይሰማዋል?

 ሃይማኖትን ከንግድ ጋር መቀላቀል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። በጥንት ዘመን አምላክን እንደሚወክሉ የሚናገሩ አንዳንድ ካህናት ‘በክፍያ በማስተማራቸው’ አምላክ እንዳዘነባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሚክያስ 3:11) አምላክ እሱ የሚመለክበትን ቦታ “የዘራፊዎች ዋሻ” ያደረጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን አውግዟቸዋል።—ኤርምያስ 7:11

 እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም በሃይማኖት ስም ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ሰዎችን ይጠላል። በዘመኑ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፣ ስግብግብ ነጋዴዎች ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲነግዱ ፈቅደው ነበር። እነዚህ ነጋዴዎች ለአምልኮ ወደዚያ ይመጡ የነበሩትን ሰዎች ይበዘብዙ ነበር። ኢየሱስ በድፍረት “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!” በማለት ስግብግቦቹን ነጋዴዎች ከቤተ መቅደሱ አካባቢ አባርሯቸዋል።—ዮሐንስ 2:14-16

 ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነበት መንገድም ቢሆን የአምላክን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። (ዮሐንስ 8:28, 29) ሰዎችን ስለ አምላክ ሲያስተምር ክፍያ ጠይቆ አያውቅም። ተአምራት ሲፈጽም ለምሳሌ የተራቡትን ሲመግብ፣ የታመሙትን ሲፈውስ ሌላው ቀርቶ የሞቱትን ሲያስነሳ እንኳ ክፍያ አልጠየቀም። ኢየሱስ በአገልግሎቱ ለመበልጸግ ሞክሮ አያውቅም፤ መኖሪያ ቤት እንኳ አልነበረውም።—ሉቃስ 9:58

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምልኳቸው ከንግድ ጋር እንዳይቀላቀል ያደረጉት እንዴት ነው?

 ኢየሱስ ተከታዮቹን ለሚሰጡት ሃይማኖታዊ አገልግሎት ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳይጠይቁ ነግሯቸዋል። “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 10:8) በኋላ ላይ ክርስቲያኖች ተብለው የተጠሩት እነዚህ የኢየሱስ ተከታዮች እሱ የሰጣቸውን መመሪያ ተከትለዋል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

  •   ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ይከተለው የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት የገንዘብ ስጦታ እንዲቀበል ግብዣ ቀርቦለት ነበር፤ ስምዖን የተባለ ሰው ለጴጥሮስ ይህንን ግብዣ ያቀረበለት ሥልጣን ማግኘት ፈልጎ ነበር። ጴጥሮስ ስጦታውን እንደማይቀበል ወዲያውኑ ገለጸ፤ እንዲያውም “የአምላክን ነፃ ስጦታ በገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ስላሰብክ የብር ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” በማለት በቆራጥነት ገሠጸው።—የሐዋርያት ሥራ 8:18-20

  •   ጳውሎስ ከቦታ ወደ ቦታ እየተጓዘ የሚያገለግል የታወቀ ሐዋርያ ነበር። በበርካታ ክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ ለዓመታት በትጋት ቢያገለግልም በአገልግሎቱ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ሞክሮ አያውቅም። እሱና ሌሎች ክርስቲያኖች ‘እንደ ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክን ቃል የሚሸቃቅጡ’ ሰዎች አልነበሩም። (2 ቆሮንቶስ 2:17) እንዲያውም ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክን ምሥራች በሰበክንላችሁ ጊዜ፣ ማናችሁንም ብዙ ወጪ በማስወጣት ሸክም እንዳንሆንባችሁ በማሰብ ሌት ተቀን እንሠራ ነበር።”—1 ተሰሎንቄ 2:9

 እርግጥ ነው እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች የስብከት ዘመቻዎች ለማካሄድና ለአንዳንድ የእርዳታ ሥራዎች የተወሰነ ገንዘብ ያስፈልጋቸው ነበር። ያም ቢሆን ለሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ክፍያ ጠይቀው አያውቁም። አንድ ሰው ከፈለገ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይችል ነበር፤ ግን ይህን የሚያደርገው በሚከተሉት መመሪያዎች መሠረት ነው፦

  •   2 ቆሮንቶስ 8:12 “ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለምና።”

     ትርጉሙ፦ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግለሰቡ የሚሰጠው የገንዘብ መጠን ሳይሆን ለመስጠት የተነሳሳበት ምክንያት ነው።

  •   2 ቆሮንቶስ 9:7 “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።”

     ትርጉሙ፦ አምላክ ማንም ሰው ተገድዶ እንዲሰጥ አይፈልግም። እሱ የሚደሰተው አንድ ሰው በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ሲሰጥ ነው።

ስግብግብ ሃይማኖቶች በቅርቡ ምን ይጠብቃቸዋል?

 አምላክ የሚቀበለው ሁሉንም ዓይነት ሃይማኖት ወይም አምልኮ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ማቴዎስ 7:21-23) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝ አንድ አስገራሚ ትንቢት የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በጠቅላላ ከአንዲት አመንዝራ ጋር ያመሳስላቸዋል፤ በዚህ መንገድ የተገለጹት፣ እነዚህ ድርጅቶች ለገንዘብ ወይም ለሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ሲሉ ከመንግሥታት ጋር ጥምረት ስለሚፈጥሩና በመላው ዓለም ያሉ ሰዎችን ስለሚበዘብዙ ነው። (ራእይ 17:1-3፤ 18:3) ይህ ትንቢት ቀጥሎ እንደሚገልጸው፣ አምላክ በቅርቡ በሐሰት ሃይማኖት ላይ እርምጃ ይወስዳል።—ራእይ 17:15-17፤ 18:7

 እስከዚያው ግን አምላክ፣ የሐሰት ሃይማኖቶች በሚፈጽሙት መጥፎ ድርጊት የተነሳ ሰዎች እንዲታለሉ ወይም ከእሱ እንዲርቁ አይፈልግም። (ማቴዎስ 24:11, 12) ቅን የሆኑ ሰዎች ተቀባይነት ባለው መንገድ እሱን ማምለክ ስለሚችሉበት መንገድ እንዲማሩና ከሐሰት ሃይማኖት እንዲወጡ ያበረታታል።—2 ቆሮንቶስ 6:16, 17