ኢሳይያስ 44:1-28

  • አምላክ የመረጠው ሕዝብ የሚያገኘው በረከት (1-5)

  • ከይሖዋ በቀር ሌላ አምላክ የለም (6-8)

  • ሰው ሠራሽ ጣዖታት ከንቱ ናቸው (9-20)

  • እስራኤልን የሚቤዠው ይሖዋ (21-23)

  • በቂሮስ አማካኝነት ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ (24-28)

44  “አሁን ግን፣ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፣የመረጥኩህም እስራኤል ሆይ፣+ ስማ።   የሠራህና ያበጀህ፣+ከማህፀን* ጀምሮ የረዳህይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘አገልጋዬ ያዕቆብ፣የመረጥኩህም የሹሩን*+ ሆይ፣ አትፍራ።+   ለተጠማው* ውኃ አፈሳለሁና፤+በደረቁ ምድርም ላይ ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ። መንፈሴን በዘርህ ላይ፣በረከቴንም በልጅ ልጆችህ ላይ አፈሳለሁ።+   እነሱም በለምለም ሣር መካከል፣በጅረቶችም ዳር እንዳሉ የአኻያ ዛፎች ይበቅላሉ።+   አንዱ “እኔ የይሖዋ ነኝ” ይላል።+ ሌላውም ራሱን በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ሌላው ደግሞ በእጁ ላይ “የይሖዋ ነኝ” ብሎ ይጽፋል። ደግሞም ራሱን በእስራኤል ስም ይጠራል።’   የእስራኤል ንጉሥ+ የሆነውና እስራኤልን የተቤዠው+ ይሖዋ፣የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የመጀመሪያው እኔ ነኝ፤ የመጨረሻውም እኔ ነኝ።+ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።+   እንደ እኔ ያለ ማን ነው?+ በድፍረት ይናገር፤ ያሳውቅም፤ ማስረጃውንም ለእኔ ያቅርብ!+ የጥንቱን ሕዝብ ካቋቋምኩበት ጊዜ ጀምሮ፣በቅርቡ የሚከሰቱትንናወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይናገሩ።   ስጋት አይደርባችሁ፤በፍርሃትም አትሽመድመዱ።+ አስቀድሜ ለእያንዳንዳችሁ አልነገርኳችሁም? ደግሞስ አላሳወቅኳችሁም? እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ።+ ከእኔ ሌላ አምላክ አለ? በፍጹም፣ ሌላ ዓለት የለም፤+ እኔ የማውቀው አንድም የለም።’”   የተቀረጹ ምስሎችን የሚሠሩ ሁሉ ከንቱ ናቸው፤የሚወዷቸውም ጣዖቶች ምንም ጥቅም የላቸውም።+ እንደ ምሥክሮቻቸው እነሱም* ምንም አያዩም፤ ምንም አያውቁም፤+በመሆኑም ሠሪዎቻቸው ለኀፍረት ይዳረጋሉ።+ 10  ለምንም የማይጠቅም አምላክ የሚሠራወይም የብረት ምስል* የሚያበጅ ማን ነው?+ 11  እነሆ፣ ባልደረቦቹ ሁሉ ያፍራሉ!+ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹ ተራ ሰዎች ናቸው። ሁሉም ተሰብስበው ይቁሙ። በፍርሃት ይዋጣሉ፤ ሁሉም ያፍራሉ። 12  አንጥረኛ በመሣሪያው* ተጠቅሞ ብረቱን በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል። ብርቱ በሆነው ክንዱበመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል።+ ከዚያም ይርበዋል፤ ጉልበትም ያጣል፤ውኃ ስለማይጠጣ ይደክማል። 13  እንጨት ጠራቢው በገመድ ይለካል፤ በቀይ ጠመኔም ንድፍ ያወጣል። በመሮም ይጠርበዋል፤ በማክበቢያም ምልክት ያደርግበታል። በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤+የሰውንም ውበት ያላብሰዋል፤ከዚያም ቤት ውስጥ* ያስቀምጠዋል።+ 14  አርዘ ሊባኖስ የሚቆርጥ ሰው አለ። እሱም አንድ የዛፍ ዝርያ ይኸውም የባሉጥ ዛፍ ይመርጣል፤እስኪጠነክርለት ድረስ በጫካው ውስጥ ባሉት ዛፎች መካከል ይተወዋል።+ የላውሮ ዛፍ ይተክላል፤ ዝናብም ያሳድገዋል። 15  ከዚያም ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል። የተወሰነውን እንጨት ወስዶ በማንደድ እሳት ይሞቃል፤እሳት አያይዞም ዳቦ ይጋግራል። ይሁንና አምላክ ሠርቶም ያመልከዋል። የተቀረጸ ምስል ሠርቶበት በፊቱ ይደፋል።+ 16  ግማሹን በእሳት ያነደዋል፤በዚያም ላይ የሚበላውን ሥጋ ይጠብሳል፤ በልቶም ይጠግባል። እሳቱንም እየሞቀ “እሰይ! እሳቱን እያየሁ ሞቅኩ” ይላል። 17  የቀረውን ግን ምስል ይቀርጽበታል፤ አምላክ አድርጎም ይሠራዋል። በፊቱም ተደፍቶ ይሰግድለታል። “አንተ አምላኬ ነህና አድነኝ” ብሎ ወደ እሱ ይጸልያል።+ 18  ምንም አያውቁም እንዲሁም አያስተውሉም፤+ምክንያቱም ዓይኖቻቸው ተጨፍነዋል፤ ማየትም አይችሉም፤ልባቸውም ማስተዋል ጎድሎታል። 19  ቆም ብሎ በልቡ ያሰበወይም እውቀትም ሆነ ማስተዋል ኖሮት እንዲህ ብሎ የተናገረ የለም፦ “ግማሹን እሳት አንድጄበታለሁ፤በፍሙም ላይ ዳቦ ጋግሬአለሁ፤ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ። ታዲያ በቀረው እንጨት አስጸያፊ ነገር መሥራቴ ተገቢ ነው?+ ከዛፍ ለተቆረጠ እንጨት* መስገድ ይገባኛል?” 20  እሱ አመድ ይበላል። የተታለለው የገዛ ልቡ አስቶታል። ራሱን* ሊያድን አይችልም፤ ደግሞም “በቀኝ እጄ ያለው ውሸት አይደለም?” አይልም። 21  “ያዕቆብ ሆይ፣ አንተም እስራኤል ሆይ፣አገልጋዬ ስለሆንክ እነዚህን ነገሮች አስታውስ። እኔ ሠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ አገልጋይ ነህ።+ እስራኤል ሆይ፣ አልረሳህም።+ 22  በደልህን በደመና፣ኃጢአትህንም ጥቅጥቅ ባለ ደመና እሸፍነዋለሁ።+ ወደ እኔ ተመለስ፤ እኔም እቤዥሃለሁ።+ 23  እናንተ ሰማያት በደስታ እልል በሉ!ይሖዋ እርምጃ ወስዷልና። እናንተ ጥልቅ የምድር ክፍሎች በድል አድራጊነት ጩኹ! እናንተ ተራሮች፣ አንተም ደን ሆይ፣በውስጡም ያላችሁ ዛፎች ሁሉ በደስታ እልል በሉ!+ ይሖዋ ያዕቆብን ተቤዥቷልና፤በእስራኤልም ላይ ግርማውን ገልጧል።”+ 24  የተቤዠህና+ ከማህፀን ጀምሮ የሠራህይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሁሉንም ነገር የሠራሁ እኔ ይሖዋ ነኝ። ብቻዬን ሰማያትን ዘረጋሁ፤+ምድርንም ሠራሁ።+ ያኔ ከእኔ ጋር ማን ነበር? 25  የሆነ ያልሆነውን የሚቀባጥሩ ሰዎችን* ምልክቶች አከሽፋለሁ፤ሟርተኞችንም ነፈዝ አደርጋለሁ፤+ጥበበኞቹንም ግራ አጋባለሁ፤እውቀታቸውንም ሞኝነት አደርጋለሁ፤+ 26  የአገልጋዬን ቃል እውን አደርጋለሁ፤የመልእክተኞቼንም ትንቢት ሙሉ በሙሉ እፈጽማለሁ፤+ስለ ኢየሩሳሌም ‘የሰው መኖሪያ ትሆናለች’፤+ ስለ ይሁዳ ከተሞችም ‘ዳግም ይገነባሉ፤+ፍርስራሾቿንም መልሼ እሠራለሁ’+ እላለሁ፤ 27  ጥልቁን ውኃ ‘ደረቅ ሁን፤ወንዞችህንም ሁሉ አደርቃለሁ’+ እላለሁ፤ 28  ስለ ቂሮስ+ ‘እሱ እረኛዬ ነው፤ፈቃዴንም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል’+ እላለሁ፤ስለ ኢየሩሳሌም ‘ዳግም ትገነባለች’፤ ስለ ቤተ መቅደሱም ‘መሠረትህ ይጣላል’+ እላለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ከተወለድክበት ጊዜ።”
“ቅን የሆነ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ለእስራኤል የተሰጠ የማዕረግ ስም ነው።
ወይም “ለተጠማው ምድር።”
ምስሎቹን ያመለክታል።
ወይም “ቀልጦ የተሠራ ሐውልት።”
ወይም “በገጀራው።”
ወይም “በአምልኮ ቦታው።”
ወይም “ከዛፍ ተቆርጦ ለደረቀ ጉማጅ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “የሐሰተኛ ነቢያትን።”