ኢዮብ 34:1-37

  • ኤሊሁ፣ የአምላክ ፍትሕና መንገድ ትክክል መሆኑን ገለጸ (1-37)

    • ኢዮብ፣ አምላክ ፍትሕ እንደነፈገው ተናግሯል (5)

    • እውነተኛው አምላክ ክፋት አይሠራም (10)

    • ኢዮብ እውቀት ይጎድለዋል (35)

34  ኤሊሁም መልስ መስጠቱን በመቀጠል እንዲህ አለ፦   “እናንተ ጥበበኞች፣ ቃሌን አዳምጡ፤እናንተ ብዙ እውቀት ያላችሁ ስሙኝ።   ምላስ* የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣ጆሮም ቃላትን ያመዛዝናል።   ትክክለኛ የሆነውን ነገር እናመዛዝን፤መልካም የሆነውን ነገር በመካከላችን እንወስን።   ኢዮብ እንዲህ ብሏልና፦ ‘እኔ ትክክል ነኝ፤+አምላክ ግን ፍትሕ ነፍጎኛል።+   ሊበየንብኝ የሚገባውን ፍርድ በተመለከተ እዋሻለሁ? በደል ባልሠራም እንኳ በላዬ ላይ ያለው ቁስል የማይሽር ነው።’+   ፌዝን እንደ ውኃ የሚጠጣ፣እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?   ክፉ ድርጊት ከሚፈጽሙ ጋር ተወዳጅቷል፤ከክፉዎችም ጋር ገጥሟል።+   ኢዮብ ‘ሰው አምላክን ለማስደሰት መሞከሩምንም ፋይዳ የለውም’ ብሏልና።+ 10  ስለዚህ እናንተ አስተዋዮች* ስሙኝ፦ ‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!+ 11  ለሰው እንደ ሥራው ይከፍለዋልና፤+መንገዱም ያስከተለበትን መዘዝ እንዲቀበል ያደርገዋል። 12  በእርግጥም አምላክ ክፋት አይሠራም፤+ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ፍትሕን አያዛባም።+ 13  ምድርን እንዲገዛ ያደረገው ማን ነው?በመላው ዓለም* ላይ የሾመውስ ማን ነው? 14  እሱ ትኩረቱን* በእነሱ ላይ ቢያደርግ፣መንፈሳቸውንና እስትንፋሳቸውን ወደ ራሱ ቢሰበስብ፣+ 15  ሰዎች* ሁሉ በአንድነት በጠፉ፣የሰውም ዘር ወደ አፈር በተመለሰ ነበር።+ 16  ስለዚህ ማስተዋል ካለህ ለዚህ ነገር ትኩረት ስጥ፤የምናገረውንም በጥሞና አዳምጥ። 17  ፍትሕን የሚጠላ ሰው፣ ገዢ ሊሆን ይገባል?ወይስ ጻድቅ የሆነውን ኃያል ሰው ትኮንነዋለህ? 18  ንጉሥን ‘የማትረባ ነህ፣’ ታላላቅ የሆኑ ሰዎችንስ ‘ክፉዎች ናችሁ’ ትላለህ?+ 19  አምላክ ለመኳንንት አያዳላም፤ሀብታሙንም ከድሃው* አስበልጦ አይመለከትም፤+ሁሉም የእጁ ሥራዎች ናቸውና።+ 20  እነሱ በእኩለ ሌሊት ድንገት ሊሞቱ ይችላሉ፤+በኃይል ተንቀጥቅጠው ሕይወታቸው ያልፋል፤ኃያላን የሆኑትም እንኳ ይወገዳሉ፤ ይሁንና ይህ የሚሆነው በሰው እጅ አይደለም።+ 21  የአምላክ ዓይኖች የሰውን መንገድ ይመለከታሉና፤+ደግሞም እርምጃውን ሁሉ ያያል። 22  ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የሚደበቁበትጨለማም ሆነ ፅልማሞት የለም።+ 23  አምላክ፣ ማንኛውም ሰው በፊቱ ለፍርድ እንዲቀርብ፣የተወሰነ ጊዜ አልቀጠረምና። 24  ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልገው ኃያላንን ይሰባብራል፤በእነሱም ቦታ ሌሎችን ይተካል።+ 25  እያደረጉ ያሉትን ያውቃልና፤+በሌሊት ይገለብጣቸዋል፤ እነሱም ይደቅቃሉ።+ 26  በክፋታቸው የተነሳ፣ሁሉም ማየት በሚችልበት ቦታ ይመታቸዋል፤+ 27  ምክንያቱም እሱን ከመከተል ወደኋላ ብለዋል፤+መንገዶቹንም ሁሉ ችላ ብለዋል፤+ 28  ድሃው ወደ እሱ እንዲጮኽ ያደርጋሉ፤እሱም የምስኪኖችን ጩኸት ይሰማል።+ 29  አምላክ ዝም ሲል ማን ሊወቅሰው ይችላል? ፊቱን በሚሰውርበት ጊዜ ማን ሊያየው ይችላል? ይህን ያደረገው በአንድ ብሔር ላይም ሆነ በአንድ ሰው ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም፤ 30  ይህም አምላክ የለሽ የሆነ* ሰው እንዳይገዛ፣+ወይም በሕዝቡ ላይ ወጥመድ እንዳይዘረጋ ነው። 31  አምላክን እንዲህ የሚል ሰው ይኖራል?‘የሠራሁት ጥፋት ባይኖርም ተቀጥቻለሁ፤+ 32  ማየት የተሳነኝን ነገር አስተምረኝ፤የሠራሁት ጥፋት ካለ ዳግመኛ አልሠራም።’ 33  ፍርዱን አልቀበልም ስትል አንተ በምትፈልገው መንገድ ሊክስህ ይገባል? መወሰን ያለብህ አንተ እንጂ እኔ አይደለሁም። ስለዚህ አንተ በደንብ የምታውቀውን ነገር ንገረኝ። 34  አስተዋይ የሆኑ* ሰዎች፣ደግሞም እኔን የሚሰሙ ጥበበኛ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሉኛል፦ 35  ‘ኢዮብ ያለእውቀት ይናገራል፤+ቃሉም ማስተዋል የጎደለው ነው።’ 36  ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ ይፈተን!*እንደ ክፉ ሰዎች መልስ ሰጥቷልና። 37  በኃጢአቱ ላይ ዓመፅ ጨምሯል፤+በፊታችን በንቀት አጨብጭቧል፤በእውነተኛውም አምላክ ላይ ብዙ ነገር ተናግሯል!”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ላንቃ።”
ቃል በቃል “እናንተ ልብ (ያላችሁ ሰዎች)።”
ወይም “ሰው በሚኖርበት ምድር።”
ቃል በቃል “ልቡን።”
ቃል በቃል “ሥጋ።”
ወይም “የተከበረውን ከችግረኛው።”
ወይም “ከሃዲ።”
ቃል በቃል “ልብ (ያላቸው)።”
“አባቴ ሆይ፣ ኢዮብ እስከ መጨረሻው ድረስ ይፈተን” ማለትም ሊሆን ይችላል።