ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-32

  • በክርስቶስ አካል አንድ መሆን (1-16)

    • ‘ሰዎችን ስጦታ አድርጎ ሰጠ’ (8)

  • አሮጌውና አዲሱ ስብዕና (17-32)

4  እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንኩ+ እኔ ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤+  በፍጹም ትሕትናና+ ገርነት፣ በትዕግሥት+ እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤+  አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።+  እናንተ የተጠራችሁበት አንድ ተስፋ+ እንዳለ ሁሉ አንድ አካልና+ አንድ መንፈስ+ አለ፤  አንድ ጌታ፣+ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ፤  ደግሞም ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በሁሉም አማካኝነት የሚሠራና በሁሉም ላይ የሚሠራ የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።  ደግሞም ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል፤ ይህን የተቀበልነው ክርስቶስ ነፃ ስጦታውን ባከፋፈለን መሠረት ነው።+  እንዲህ ይላልና፦ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮኞችን ወሰደ፤ ሰዎችንም ስጦታ አድርጎ ሰጠ።”+  ታዲያ “ወደ ላይ ወጣ” የሚለው አነጋገር ምን ማለት ነው? ወደ ታች ይኸውም ወደ ምድርም ወርዷል ማለት ነው። 10  ሁሉንም ነገር ወደ ሙላት ያደርስ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ+ የወጣው+ ያው ወደ ታች የወረደው ራሱ ነው። 11  እንዲሁም አንዳንዶቹን ሐዋርያት፣+ አንዳንዶቹን ነቢያት፣+ አንዳንዶቹን ወንጌላውያን፣*+ አንዳንዶቹን ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች+ አድርጎ ሰጠ፤ 12  ይህን ያደረገው ቅዱሳንን እንዲያስተካክሉ፣* ሌሎችን እንዲያገለግሉና የክርስቶስን አካል* እንዲገነቡ ነው፤+ 13  ይህም ሁላችንም በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆን*+ ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ ነው። 14  በመሆኑም ከእንግዲህ ሕፃናት መሆን የለብንም፤ በማዕበል የምንነዳ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣+ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ የምንንገዋለልና ወዲያና ወዲህ የምንል መሆን የለብንም። 15  ከዚህ ይልቅ እውነትን በመናገር በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ+ በፍቅር እንደግ። 16  በእሱ አማካኝነት የአካል ክፍሎች ሁሉ+ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል። እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።+ 17  ስለዚህ አሕዛብ በአእምሯቸው ከንቱነት*+ እንደሚመላለሱ እናንተም ከእንግዲህ እንዳትመላለሱ በጌታ እናገራለሁ እንዲሁም እመሠክራለሁ።+ 18  እነሱ በውስጣቸው ካለው ድንቁርናና ከልባቸው መደንደን የተነሳ አእምሯቸው ጨልሟል፤ እንዲሁም ከአምላክ ከሚገኘው ሕይወት ርቀዋል። 19  የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ማንአለብኝነት ለሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ አሳልፈው ሰጥተዋል። 20  እናንተ ግን ክርስቶስ እንዲህ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 21  ይህ ሊሆን የሚችለው በእርግጥ ኢየሱስ ካስተማረው እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ከሰማችሁና ከእሱ ከተማራችሁ ነው። 22  ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን+ አሮጌውን ስብዕናችሁን* አውልቃችሁ እንድትጥሉ+ ተምራችኋል። 23  ደግሞም አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል* እየታደሰ ይሂድ፤+ 24  እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና* መልበስ ይኖርባችኋል።+ 25  ስለዚህ አሁን አታላይነትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ* ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤+ ምክንያቱም ሁላችንም የአንድ አካል ክፍሎች ነን።+ 26  ተቆጡ፤ ሆኖም ኃጢአት አትሥሩ፤+ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤+ 27  ዲያብሎስ አጋጣሚ እንዲያገኝ አታድርጉ።*+ 28  የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።+ 29  እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል ብቻ+ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።+ 30  በተጨማሪም በቤዛው ነፃ ለምትወጡበት+ ቀን የታተማችሁበትን+ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አታሳዝኑ።+ 31  የመረረ ጥላቻ፣+ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ+ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ።+ 32  ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤+ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች።”
ወይም “እንዲያሠለጥኑ።”
የክርስቶስን ተከታዮች ጉባኤ ያመለክታል።
ወይም “ወደ ጉልምስና።”
ወይም “ባዶነት።”
ወይም “እፍረተ ቢስነት ለሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሰው።”
ወይም “አስተሳሰባችሁ።” ቃል በቃል “የአእምሯችሁ መንፈስ።”
ቃል በቃል “ሰው።”
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “ዲያብሎስ ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት።”