ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:1-66

  • ኤርምያስ ስሜቱንና ተስፋውን ገለጸ

    • “በትዕግሥት እጠባበቃለሁ” (21)

    • የአምላክ ምሕረት በየማለዳው አዲስ ነው (22, 23)

    • ይሖዋ በእሱ ተስፋ ለሚያደርግ ሰው ጥሩ ነው (25)

    • በልጅነት ቀንበር መሸከም ጥሩ ነው (27)

    • አምላክ ወደ እሱ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በደመና ዘግቷል (43, 44)

א [አሌፍ] 3  እኔ ከቁጣው በትር የተነሳ መከራ ያየሁ ሰው ነኝ።   ወደ ውጭ አስወጥቶኛል፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ ውስጥ እንድሄድ አድርጎኛል።+   ቀኑን ሙሉ በተደጋጋሚ እጁን በእኔ ላይ ሰነዘረ።+ ב [ቤት]   ሥጋዬና ቆዳዬ እንዲያልቅ አደረገ፤አጥንቶቼን ሰባበረ።   ቅጥር ሠራብኝ፤ በመራራ መርዝና+ በመከራ ዙሪያዬን ከበበኝ።   ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው ሰዎች፣ በጨለማ ስፍራዎች እንድቀመጥ አስገደደኝ። ג [ጊሜል]   ማምለጥ እንዳልችል በቅጥር ዘጋብኝ፤ከመዳብ በተሠራ ከባድ የእግር ብረት አሰረኝ።+   ደግሞም እርዳታ ለማግኘት አምርሬ ስጮኽ ጸሎቴን አይሰማም።*+   መንገዶቼን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ጎዳናዎቼን አጣመመ።+ ד [ዳሌት] 10  እንደ ድብ፣ እንዳደፈጠ አንበሳም አድብቶ ይጠብቀኛል።+ 11  ከመንገድ ገፍትሮ አስወጣኝ፤ ገነጣጠለኝም፤*ወና አስቀረኝ።+ 12  ደጋኑን ወጠረ፤* የፍላጻውም ዒላማ አደረገኝ። ה [] 13  ኮሮጆው ውስጥ በያዛቸው ፍላጻዎች* ኩላሊቴን ወጋ። 14  የሕዝብ ሁሉ ማላገጫ ሆንኩ፤ ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ እየዘፈኑ ይሳለቁብኛል። 15  መራራ ነገሮችን እስኪበቃኝ ድረስ አበላኝ፤ ጭቁኝም አጠገበኝ።+ ו [ዋው] 16  ጥርሶቼን በጠጠር ይሰብራል፤አመድ ላይ ይጥለኛል።+ 17  ሰላም ነፈግከኝ፤* ጥሩ ነገር ምን እንደሆነ እንኳ ረሳሁ። 18  ስለዚህ “ግርማ ሞገሴ ተገፏል፤ ከይሖዋ የጠበቅኩት ነገርም ጠፍቷል” እላለሁ። ז [ዛየን] 19  መጎሳቆሌንና ዱር አዳሪ* መሆኔን እንዲሁም ጭቁኝና መራራ መርዝ መብላቴን አስታውስ።+ 20  አንተ በእርግጥ ታስታውሳለህ፤* እኔን ለመርዳትም ታጎነብሳለህ።+ 21  ይህ ከልቤ አይጠፋም፤ ከዚህም የተነሳ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።+ ח [ኼት] 22  ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር የተነሳ ሙሉ በሙሉ አልጠፋንም፤+ምሕረቱ ፈጽሞ አያልቅምና።+ 23  በየማለዳው አዲስ ነው፤+ ታማኝነትህ እጅግ ብዙ ነው።+ 24  እኔ “ይሖዋ ድርሻዬ ነው”+ አልኩ፤* “እሱን በትዕግሥት የምጠባበቀው ለዚህ ነው።”+ ט [ቴት] 25  ይሖዋ በእሱ ተስፋ ለሚያደርግ፣+ እሱንም ዘወትር ለሚሻ ሰው* ጥሩ ነው።+ 26  የይሖዋን ማዳን+ ዝም ብሎ* መጠባበቅ ጥሩ ነው።+ 27  ሰው በልጅነቱ ቀንበር ቢሸከም ጥሩ ነው።+ י [ዮድ] 28  አምላክ ቀንበሩን በእሱ ላይ ሲጥልበት ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።+ 29  ፊቱን አቧራ ውስጥ ይቅበር፤+ ገና ተስፋ ሊኖር ይችላል።+ 30  ጉንጩን፣ ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ስድብንም ይጥገብ። כ [ካፍ] 31  ይሖዋ ለዘላለም አይጥለንምና።+ 32  ለሐዘን የዳረገን ቢሆንም እንኳ እንደ ታማኝ ፍቅሩ ብዛት ምሕረት ያሳያል።+ 33  የልቡ ፍላጎት የሰው ልጆች እንዲጎሳቆሉ ወይም እንዲያዝኑ ማድረግ አይደለምና።+ ל [ላሜድ] 34  የምድር እስረኞች ሁሉ በእግር ሲረገጡ፣+ 35  በልዑል አምላክ ፊት ሰው ፍትሕ ሲነፈግ፣+ 36  ሰው ከፍርድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲጭበረበር፣ይሖዋ እንዲህ ያለውን ነገር በቸልታ አያልፍም። מ [ሜም] 37  ይሖዋ ካላዘዘ በቀር አንድን ነገር ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው? 38  ከልዑሉ አምላክ አፍክፉ ነገርና መልካም ነገር በአንድነት አይወጣም። 39  ሕያው የሆነ ሰው ኃጢአቱ ባስከተለበት መዘዝ ለምን ያጉረመርማል?+ נ [ኑን] 40  መንገዳችንን እንመርምር፤ ደግሞም እንፈትን፤+ ከዚያም ወደ ይሖዋ እንመለስ።+ 41  በሰማያት ወዳለው አምላክ እጃችንን ዘርግተን ከልብ የመነጨ ልመና እናቅርብ፦+ 42  “እኛ በድለናል፤ ደግሞም ዓምፀናል፤+ አንተም ይቅር አላልክም።+ ס [ሳሜኽ] 43  ጨርሶ እንዳንቀርብ በቁጣ አገድከን፤+አሳደድከን፤ ያለርኅራኄም ገደልከን።+ 44  ጸሎታችን እንዳያልፍ ወደ አንተ መቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በደመና ዘጋህ።+ 45  በሕዝቦች መካከል ጥራጊና ቆሻሻ አደረግከን።” פ [] 46  ጠላቶቻችን ሁሉ በእኛ ላይ አፋቸውን ከፈቱ።+ 47  ፍርሃትና ወጥመድ፣ ባድማነትና ጥፋት ዕጣ ፋንታችን ሆነ።+ 48  ከሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት የተነሳ ዓይኔ የእንባ ጎርፍ አፈሰሰ።+ ע [አይን] 49  ዓይኖቼ ያለማቋረጥና ያለእረፍት ያነባሉ፤+ 50  ይሖዋ ከሰማይ ወደ ታች እስኪያይና እስኪመለከት ድረስ ያነባሉ።+ 51  በከተማዬ ሴቶች ልጆች* ሁሉ ላይ የደረሰውን በማየቴ አዘንኩ።*+ צ [ጻዴ] 52  ጠላቶቼ ያለምክንያት እንደ ወፍ አደኑኝ። 53  ሕይወቴን በጉድጓድ ውስጥ ጸጥ ሊያደርጓት ሞከሩ፤ በላዬም ላይ የድንጋይ ናዳ ያወርዱብኛል። 54  በራሴ ላይ ውኃ ጎረፈ፤ እኔም “አለቀልኝ!” አልኩ። ק [ኮፍ] 55  ይሖዋ ሆይ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ስምህን ጠራሁ።+ 56  ድምፄን ስማ፤ እርዳታና እፎይታ ለማግኘት የማሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮህን አትድፈን። 57   በጠራሁህ ቀን ወደ እኔ ቀረብክ። “አትፍራ” አልከኝ። ר [ረሽ] 58  ይሖዋ ሆይ፣ ተሟገትክልኝ፤* ሕይወቴን ዋጀህ።+ 59  ይሖዋ ሆይ፣ በእኔ ላይ የደረሰውን በደል አይተሃል፤ እባክህ ፍትሕ እንዳገኝ አድርግ።+ 60  በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ተመልክተሃል። ש [ሲን] ወይም [ሺን] 61  ይሖዋ ሆይ፣ ዘለፋቸውን፣ በእኔም ላይ ያሴሩትን ሁሉ ሰምተሃል፤+ 62  ከባላንጣዎቼ አፍ የሚወጣውን ቃልና ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ የሚያንሾካሹኩትን ነገር ሰምተሃል። 63  እያቸው፤ ተቀምጠውም ሆነ ቆመው በዘፈናቸው ይሳለቁብኛል! ת [ታው] 64  ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ሥራቸው መልሰህ ትከፍላቸዋለህ። 65  እርግማንህን በእነሱ ላይ በማውረድ ደንዳና ልብ እንዲኖራቸው ታደርጋለህ። 66  ይሖዋ ሆይ፣ በቁጣ ታሳድዳቸዋለህ፤ ከሰማያትህም በታች ታጠፋቸዋለህ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አገደ፤ ከለከለ።”
“ያልታረሰም መሬት አደረገኝ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ረገጠ።”
ቃል በቃል “ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ነፍሴን ሰላም ነፈግካት።”
ወይም “ቤት የለሽ።”
ወይም “ነፍስህ በእርግጥ ታስታውሳለች።”
ወይም “ነፍሴ ‘ይሖዋ ድርሻዬ ነው’ አለች።”
ወይም “ለምትሻ ነፍስ።”
ወይም “በትዕግሥት።”
ወይም “በከተማዬ ዙሪያ ባሉ ከተሞች።”
ወይም “ነፍሴ አዘነች።”
ወይም “ለነፍሴ ተሟገትክላት።”