የሐዋርያት ሥራ 17:1-34

  • ጳውሎስና ሲላስ በተሰሎንቄ (1-9)

  • ጳውሎስና ሲላስ በቤርያ (10-15)

  • ጳውሎስ በአቴንስ (16-22ሀ)

  • ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ያቀረበው ንግግር (22ለ-34)

17  ከዚያም በአምፊጶሊስና በአጶሎንያ በኩል ተጉዘው የአይሁዳውያን ምኩራብ ወዳለበት ወደ ተሰሎንቄ መጡ።+  ጳውሎስም እንደ ልማዱ+ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ለሦስት ሰንበትም ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤+  ክርስቶስ መከራ መቀበሉና+ ከሞት መነሳቱ+ አስፈላጊ እንደነበር ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት “ይህ እኔ የማውጅላችሁ ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ ነው” አላቸው።  ከዚህም የተነሳ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ አማኞች በመሆን ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ፤+ ከግሪካውያንም መካከል አምላክን የሚያመልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የታወቁ ሴቶች እንዲሁ አደረጉ።  ሆኖም አይሁዳውያን ቅናት ስላደረባቸው+ በገበያ ስፍራ የሚያውደለድሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አሰባስበው አሳደሙ፤ ከተማዋንም በሁከት አመሷት። ጳውሎስንና ሲላስንም አምጥተው ለረብሻ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ለማቅረብ የያሶንን ቤት ሰብረው ገቡ።  ባጧቸው ጊዜም ያሶንንና አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦ “ዓለምን ሁሉ ያናወጡት* እነዚያ ሰዎች እዚህም መጥተዋል፤+  ያሶንም በእንግድነት ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።”+  ሕዝቡና የከተማዋ ገዢዎች ይህን ሲሰሙ ተሸበሩ፤  ያሶንን እና ሌሎቹን የዋስትና ገንዘብ እንዲያስይዙ ካደረጓቸው በኋላ* ለቀቋቸው። 10  ወንድሞችም እንደመሸ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤርያ ላኳቸው። እነሱም እዚያ እንደደረሱ ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገቡ። 11  በቤርያ የነበሩት አይሁዳውያን በተሰሎንቄ ከነበሩት ይልቅ ቀና አስተሳሰብ ስለነበራቸው የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀበሉ። 12  ስለዚህ ከእነሱ መካከል ብዙዎቹ እንዲሁም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የተከበሩ ግሪካውያን ሴቶችና የተወሰኑ ወንዶች አማኞች ሆኑ። 13  ሆኖም በተሰሎንቄ ያሉት አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ቃል በቤርያም እንዳወጀ ባወቁ ጊዜ ሕዝቡን ለማነሳሳትና ለማወክ ወደዚያ መጡ።+ 14  በዚህ ጊዜ ወንድሞች ወዲያውኑ ጳውሎስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ላኩት፤+ ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን እዚያው ቀሩ። 15  ጳውሎስን የሸኙት ሰዎችም እስከ አቴንስ አደረሱት፤ ከዚያም ጳውሎስ ‘ሲላስና ጢሞቴዎስ+ በተቻለ ፍጥነት ወደ እኔ እንዲመጡ ንገሯቸው’ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፤ ሰዎቹም ተመልሰው ሄዱ። 16  ጳውሎስ በአቴንስ እየጠበቃቸው ሳለ ከተማዋ በጣዖት የተሞላች መሆኗን አይቶ መንፈሱ ተረበሸ። 17  ስለዚህ በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር እንዲሁም በየዕለቱ በገበያ ስፍራ* ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ ጀመር። 18  ሆኖም ከኤፊቆሮስና ከኢስጦይክ ፈላስፎች መካከል አንዳንዶቹ ይከራከሩት ጀመር፤ ሌሎቹ ደግሞ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊያወራ ፈልጎ ነው?” ይሉ ነበር። “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚያውጅ ይመስላል” የሚሉም ነበሩ። ይህን ያሉት ስለ ኢየሱስና ስለ ትንሣኤ የሚገልጸውን ምሥራች ያውጅ ስለነበር ነው።+ 19  ስለዚህ ይዘው ወደ አርዮስፋጎስ* ከወሰዱት በኋላ እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምትናገረው አዲስ ትምህርት ምን እንደሆነ ልታስረዳን ትችላለህ? 20  ምክንያቱም ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው፤ ይህ ነገር ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን።” 21  የአቴንስ ሰዎችና በዚያ የሚገኙ* የባዕድ አገር ሰዎች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት ብቻ ነበር። 22  በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ+ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፦ “የአቴንስ ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም ነገር ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ* ማየት ችያለሁ።+ 23  ለአብነት ያህል፣ እየተዘዋወርኩ ሳለሁ የምታመልኳቸውን ነገሮች በትኩረት ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። ስለዚህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ አሳውቃችኋለሁ። 24  ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ+ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም፤+ 25  በተጨማሪም ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው+ እሱ ስለሆነ የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም።+ 26  በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም+ የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤+ የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤+ 27  ይህን ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤+ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም። 28  ምክንያቱም ከእናንተ ባለቅኔዎች አንዳንዶቹ ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው እንደተናገሩት ሁሉ ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው። 29  “እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች+ ከሆንን አምላክ በሰው ጥበብና ንድፍ ከወርቅ፣ ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።+ 30  እርግጥ አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ+ ችላ ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ ነው። 31  ምክንያቱም በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ+ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህን ለማድረግም ቀን ወስኗል፤ እሱንም ከሞት በማስነሳት ለሰዎች ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።”+ 32  እነሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር፤+ ሌሎቹ ግን “ስለዚሁ ጉዳይ በድጋሚ መስማት እንፈልጋለን” አሉት። 33  በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ 34  አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ። ከእነሱም መካከል የአርዮስፋጎስ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ዲዮናስዮስና ደማሪስ የተባለች ሴት እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ያወኩት።”
ወይም “ዋስ ተቀብለው።”
ሰዎች የሚገበያዩበት እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባ የሚካሄድበት ገላጣ ስፍራ።
በጥንቷ አቴና የሚገኝ ኮረብታ ሲሆን በዚህ ቦታ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ይሰበሰብ ነበር።
ወይም “ለጉብኝት የመጡ።”
ወይም “ሃይማኖተኞች እንደሆናችሁ።”