በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?

ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?

 ሰውነትን መቁረጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

 ሰውነትን መቁረጥ የሚለው አገላለጽ፣ በሰውነት ላይ ሆን ብሎ በስለት ጉዳት የማድረስ ልማድን ያመለክታል። ይህ፣ ራሳቸውን የመጉዳት ልማድ ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት አንዱ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ ሰውነታቸውን ሊያቃጥሉ ወይም እስኪበልዝ ድረስ ራሳቸውን ሊመቱ ይችላሉ። በዚህ ርዕስ ላይ የሚብራራው፣ ሰውነትን ስለ መቁረጥ ቢሆንም ነጥቦቹ በሌሎች መንገዶች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ለሚያደርሱ ሰዎችም ይሠራሉ።

 እውቀትሽን ፈትሺ፦ እውነት ወይስ ሐሰት?

  1.   ሰውነታቸውን የሚቆርጡት ሴቶች ብቻ ናቸው።

  2.   ሰውነትን መቁረጥ፣ በዘሌዋውያን 19:28 (የ1980 ትርጉም) ላይ ከሚገኘው “ሰውነታችሁን አትቈራርጡ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር ይጋጫል።

 መልስ፦

  1.   ሐሰት። ይህ ችግር በአብዛኛው የሚታየው በሴቶች ላይ ቢሆንም አንዳንድ ወንዶችም ሰውነታቸው ይቆርጣሉ ወይም በሌሎች መንገዶች በራሳቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።

  2.   ሐሰት። ዘሌዋውያን 19:28 የሚናገረው በጥንት ዘመን ይከናወን ስለነበረ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት እንጂ በዚህ ርዕስ ላይ ስለሚብራራው በሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስ ልማድ አይደለም። ያም ቢሆን አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን በራሳችን ላይ ጉዳት እንድናደርስ አይፈልግም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 6:12፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ 1 ዮሐንስ 4:8

 ምክንያቱ ምንድን ነው?

 እውቀትሽን ፈትሺ፦ ትክክል የሆነው ዓረፍተ ነገር የትኛው ነው?

 ሰዎች፣ ሰውነታቸውን የሚቆርጡት . . .

  1.  ሀ. በውስጣቸው ያለውን የስሜት ሥቃይ እንደሚያስታግሥላቸው ስለሚያስቡ ነው።

  2.  ለ. ሕይወታቸውን ለማጥፋት አስበው ነው።

 መልስ፦ ሀ. ሰውነታቸውን የሚቆርጡ አብዛኞቹ ሰዎች መሞት አይፈልጉም። ይህን የሚያደርጉት በውስጣቸው የሚሰማቸውን ሥቃይ ለማስቆም ስለሚፈልጉ ነው።

 ሰውነታቸውን የመቁረጥ ልማድ የነበራቸው አንዳንድ ወጣቶች የተናገሩትን ተመልከቺ።

 ሲልያ፦ “እፎይ እንድል ያደርገኝ ነበር።”

 ታማራ፦ “ከሥቃዩ የሚገላግለኝ ይመስለኝ ነበር። በውስጤ ከሚሰማኝ ሥቃይ ይልቅ ሰውነቴ መቆረጡ የሚያስከትለውን ሕመም እመርጥ ነበር።”

 ካሪ፦ “የሚሰማኝን የሐዘን ስሜት በጣም እጠላው ነበር። ሰውነቴን ስቆርጥ፣ ስለ ሐዘኔ ማሰቤን ትቼ ቁስሉ በሚያስከትልብኝ ሕመም ላይ አተኩራለሁ።”

 ጄሪን፦ “ሰውነቴን መቁረጤ በዙሪያዬ ያለውን ነገር ለመርሳት ያስችለኛል፤ እንዲህ ሳደርግ፣ ችግሮቼን መጋፈጥ እንደሌለብኝ ይሰማኛል። ትኩረቴ በሌላ ነገር ላይ እንዲያርፍ ስለሚያደርግ ደስ ይለኛል።”

 እንዲህ ያለ ችግር ካለብሽ ይህን ለማሸነፍ ምን ሊረዳሽ ይችላል?

 ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለይ፣ ችግሩን ለማሸነፍ ከፍተኛ እገዛ ያደርግልሻል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል።​—1 ጴጥሮስ 5:7

 እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ ችግሩን ለማሸነፍ መጀመሪያ አካባቢ አጠር ያለ ጸሎት ማቅረብ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ “ይሖዋ፣ እባክህ እርዳኝ” ማለት ትችያለሽ። እያደር ግን፣ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ለሆነው ለይሖዋ በልብሽ ያለውን በሙሉ አውጥተሽ መናገር ትችያለሽ።​—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

 ጸሎት፣ ለሚሰማሽ ሥቃይ ጊዜያዊ ማስታገሻ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም። በሰማይ ለሚኖረው አባትሽ የልብሽን አውጥተሽ መናገር የምትችዪበት መንገድ ነው፤ እሱ እንዲህ ብሎ ቃል ገብቶልናል፦ “እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።”​—ኢሳይያስ 41:10

 ሰውነታቸውን የመቁረጥ ችግር ያለባቸው ብዙዎች፣ የሚሰማቸውን ነገር ለወላጆቻቸው ወይም ለሚተማመኑበት ሌላ አዋቂ ሰው መናገራቸው እንዲጽናኑ ረድቷቸዋል። እንዲህ ያደረጉ ሦስት ወጣቶች ከዚህ በታች የተናገሩትን ሐሳብ እንድታነብቢ እንጋብዝሻለን።

 ልታስቢባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

  • የሌሎችን እርዳታ ለመጠየቅ ስትፈልጊ ማንን ማነጋገር ትችያለሽ?

  • ያለብሽን ችግር በተመለከተ ወደ ይሖዋ አምላክ ምን ብለሽ መጸለይ ትችያለሽ?

  • ጭንቀትሽ ቀለል እንዲልሽ የሚረዱ ሁለት መንገዶችን (በራስ ላይ ጉዳት ማድረስን ሳይጨምር) መጥቀስ ትችያለሽ?

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።