በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ይህ ሰው ይሆነኛል?

ይህ ሰው ይሆነኛል?

 ጥሩ የትዳር ጓደኛ ሊሆን እንደሚችል ያሰብሽው ሰው አለ? a ከሆነ ይህ ሰው ለትዳር እንደሚሆንሽ ማወቅ የምትችይው እንዴት ነው?

 ከውጭ በሚታዩ ባሕርያት ላይ ሳይሆን በውስጣዊ ማንነት ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው። በጣም ቆንጆ የምትባለው ሴት የምትታመን ላትሆን ትችላለች፤ አሊያም ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ወጣት ጨዋ ላይሆን ይችላል። ለትዳር የምትፈልጊው ሰው፣ የሚስማማሽ ይኸውም ከባሕርይሽ ጋር የሚጣጣምና እንደ አንቺ ዓይነት ግብ ያለው ሰው አይደለም?—ዘፍጥረት 2:18፤ ማቴዎስ 19:4-6

ውጫዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከማተኮር መቆጠብ

 ግለሰቡ ይሆንሽ እንደሆነ በምትገመግሚበት ወቅት ስሜታዊ ላለመሆን ጥንቃቄ አድርጊ! ምክንያቱም ማየት የምትፈልጊውን ብቻ ወደ ማየት ልታዘነብዪ ትችያለሽ። ስለዚህ አትቸኩዪ። የግለሰቡን እውነተኛ ባሕርያት ለማወቅ ጥረት አድርጊ።

 መጠናናት የጀመሩ ብዙ ወጣቶች ከውጫዊ ነገሮች አልፈው አይመለከቱም። ቶሎ የሚታዩዋቸው ከወደዱት ሰው ጋር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ናቸው፤ ለምሳሌ “የሙዚቃ ምርጫችን አንድ ዓይነት ነው።” “የምንመርጣቸው የጊዜ ማሳለፊያዎች ተመሳሳይ ናቸው።” “በሁሉም ነገር እንስማማለን!” ማለት ይቀናቸዋል። አንቺ ግን ውጫዊ ከሆኑ ነገሮች አልፈሽ መመልከት አለብሽ። ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልግሻል። (1 ጴጥሮስ 3:4፤ ኤፌሶን 3:16) ለምሳሌ፣ በምትስማሙባቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የማትስማሙባቸው ነገሮች ሲኖሩ ግለሰቡ ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚያሳይ ብታስተውዪ ስለ ውስጣዊ ማንነቱ ይበልጥ ማወቅ ትችያለሽ።

 እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች አስቢባቸው፦

  •   ይህ ሰው አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ምን ያደርጋል? እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ይላል? ምናልባትም “በቁጣ መገንፈል” ወይም ‘መሳደብ’ ይቀናዋል? (ገላትያ 5:19, 20፤ ቆላስይስ 3:8) ወይስ ነገሩ የምርጫ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሰላም ለመፍጠር ሲል የሌላውን ሐሳብ በመቀበል ምክንያታዊ መሆኑን ያሳያል?—ያዕቆብ 3:17

  •   ይህ ሰው የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ሲል ሊጫንሽ ይሞክራል? በትንሽ በትልቁ ይቀናል? የት ገባሽ የት ወጣሽ ያበዛል? ኒኮል እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጓደኛሞች፣ ‘ምንጊዜም ቢሆን የት እንዳለሽ ማወቅ አለብኝ’ በሚል እንደሚጨቃጨቁ እሰማለሁ። እንዲህ ያለው ባሕርይ ችግር መኖሩን የሚጠቁም ምልክት እንደሆነ ይሰማኛል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4

  •   ጓደኛሽ በሰዎች ዘንድ ምን ስም አትርፏል? ይህን ለማወቅ ግለሰቡን በደንብ የሚያውቁትን ሰዎች ለምሳሌ በጉባኤ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገሩ ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መንገድ ጓደኛሽ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” መሆን አለመሆኑን ማወቅ ትችያለሽ።—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።