በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስፖርታዊ ጨዋታዎችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ስፖርታዊ ጨዋታዎችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 ስፖርታዊ ጨዋታዎች ጥቅምም ጉዳትም አላቸው። ይህ የተመካው በምትጫወተው ጨዋታ፣ በምትጫወትበት መንገድና በመጫወት በምታሳልፈው ጊዜ ላይ ነው።

 ምን ጥቅሞች አሉት?

 ስፖርታዊ ጨዋታዎች ለጤንነት ጠቃሚ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጠቃሚ’ እንደሆነ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ራያን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣሉ። ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ የቪዲዮ ጌም ከመጫወት በጣም ይሻላል።”

 በስፖርታዊ ጨዋታዎች መካፈል ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትንና ራስን መቆጣጠርን ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ነጥብ ለማስጨበጥ፣ ስለ አንድ ስፖርታዊ ጨዋታ የሚገልጽ ምሳሌ ይጠቀማል። ምሳሌው “በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም?” ካለ በኋላ “በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 9:24, 25) ነጥቡ ምንድን ነው? የአንድን ስፖርታዊ ጨዋታ ሕግ አክብሮ ለመጫወት ራስን መግዛትና ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር መተባበር ያስፈልጋል። አቢጌል የተባለች ወጣት በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እሷም “በስፖርታዊ ጨዋታዎች መሳተፌ ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን እና መግባባትን አስተምሮኛል” ብላለች።

 በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ከሌሎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችላል። ሰዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አብረው መካፈላቸው አንድነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ጆርዳን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ስፖርታዊ ጨዋታዎች ፉክክር ይኖራቸዋል፤ ሆኖም ዓላማችሁ መዝናናት ከሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አንድ ላይ ማድረጋችሁ ግንኙነታችሁ እንዲጠናከር የሚረዳ ጥሩ መንገድ ነው።”

 ምን አደጋዎች አሉት?

 የምትጫወተው ጨዋታ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ጻድቁንም ሆነ ክፉውን ይመረምራል፤ ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል” ይላል።—መዝሙር 11:5

 አንዳንድ ጨዋታዎች በዓመፅ መንፈስ የተሞሉ ናቸው። ለምሳሌ ሎረን የተባለች አንዲት ወጣት ያስተዋለችውን ነገር እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የቦክስ ጨዋታ ዓላማ ሌላኛውን ሰው መምታት ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከሌሎች ጋር እንደማንጣላ የታወቀ ነው፤ ታዲያ ሰዎች ሲደባደቡ የሚታይበት ጨዋታ በመመልከት ለምን እንዝናናለን?”

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ዓመፅ የሚንጸባረቅበት ጨዋታ ብጫወት ወይም ብመለከት እንኳ የዓመፅ ድርጊት እንድፈጽም አያደርገኝም ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ከሆነ መዝሙር 11:5፣ ይሖዋ ክፋትን የሚያደርጉ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ‘ክፋትን የሚወዱ ሰዎችንም ይጠላል’ እንደሚል ልብ በል።

 የምትጫወትበት መንገድ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።”—ፊልጵስዩስ 2:3

 እርግጥ ነው፣ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች የሚጫወቱበት ማንኛውም ጨዋታ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ፉክክር እንደሚኖረው የታወቀ ነው። ሆኖም ‘ምንም ቢሆን ማሸነፍ አለብኝ’ የሚል አቋም ይዞ መጫወት ጨዋታው አስደሳች እንዳይሆን ያደርጋል። ብራያን የተባለ ወጣት እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በቀላሉ በፉክክር መንፈስ ልትጠመዱ ትችላላችሁ። በስፖርቱ ላይ ጎበዝ እየሆናችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ትሕትና ለማዳበር ይበልጥ ጥረት ማድረግ አለባችሁ።”

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ክሪስ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በየሳምንቱ እግር ኳስ እንጫወታለን፤ አንዳንድ ጊዜ ስንጫወት ጉዳት ያጋጥመናል።” በመሆኑም ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ለአደጋ ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርጉኝ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለአደጋ የምጋለጥበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ምን ማድረግ እችላለሁ?’

 በመጫወት የምታሳልፈው ጊዜ። መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል።—ፊልጵስዩስ 1:10

 ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መወሰን አለብህ፤ መንፈሳዊ ነገሮች ከሁሉም እንቅስቃሴዎች መቅደም አለባቸው። አብዛኞቹ ጨዋታዎች ለመጫወትም ሆነ ለመመልከት በርካታ ሰዓታት ይወስዳሉ። ዳሪያ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የተሻለ ነገር ላደርግ ስችል በቴሌቪዥን የስፖርት ጨዋታዎችን እየተመለከትኩ በርካታ ሰዓታትን ስለማሳልፍ እናቴ ትቆጣኝ ነበር።”

ለስፖርታዊ ጨዋታዎች ከልክ ያለፈ ቦታ መስጠት ምግባችሁ ውስጥ በጣም ብዙ ጨው ከመጨመር ጋር ይመሳሰላል

 ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ወላጆችህ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በተመለከተ ምክር ሲሰጡህ ትቀበላለህ? ትሪና የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ማድረግ ያሉብንን ነገሮች ችላ ብለን የስፖርት ጨዋታዎችን ስንመለከት እናታችን ‘እናንተ ጨዋታውን ተመለከታችሁም አልተመለከታችሁ ተጫዋቾቹ ደሞዝ ይከፈላቸዋል። እናንተን ግን የሚከፍላችሁ ማን ነው?’ ብላ ትጠይቀን ነበር። ማስተላለፍ የፈለገችው ነጥብ ይህ ነበር፦ ተጫዋቾቹ ሥራ አላቸው። እናንተ ግን የቤት ሥራችሁንና ሌሎች ኃላፊነቶቻችሁን የማትወጡ ከሆነ ወደፊት ሥራ ማግኘት አትችሉም። እማማ፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን መመልከት ወይም መጫወት በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያ ቦታ ሊሰጠው እንደማይገባ መናገሯ ነበር።”