በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ ያስተማረውንና ሐዋርያቱ በተግባር ያዋሉትን የክርስትና ትምህርት ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። ይህ ርዕስ የምናምንባቸውን መሠረታዊ ነገሮች ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል።

  1.   አምላክ። እውነተኛና ሁሉን ቻይ የሆነውን ይሖዋ የተባለውን አንድ አምላክ እናመልካለን። (መዝሙር 83:18፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ የአብርሃም፣ የሙሴ እና የኢየሱስ አምላክ ነው።—ዘፀአት 3:6፤ 32:11፤ ዮሐንስ 20:17

  2.   መጽሐፍ ቅዱስ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች በመንፈሱ አማካኝነት ያስጻፈው መልእክት እንደሆነ እናምናለን። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) እምነታችን የተመሠረተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በ66ቱም መጻሕፍት ላይ ነው፤ እነዚህ መጻሕፍት በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” እና “አዲስ ኪዳን” በመባል ይታወቃሉ። ፕሮፌሰር ጄሰን ቤዱን የይሖዋ ምሥክሮች “የሚያምኑበትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርጋሉ እንጂ አንድን ነገር አስቀድመው ከወሰኑ በኋላ ያንን የሚደግፍ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት አይሞክሩም” በማለት ጽፈዋል። a

     ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እንቀበላለን፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ቃል በቃል መወሰድ አለበት የሚል እምነት የለንም። የተወሰኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት በዘይቤያዊ ወይም በምሳሌያዊ አነጋገር ስለሆነ ቃል በቃል መወሰድ እንደሌለባቸው እንገነዘባለን።

  3.   ኢየሱስ። የኢየሱስን ትምህርትም ሆነ እሱ የተወውን ምሳሌ እንከተላለን፤ በተጨማሪም የአምላክ ልጅ እንዲሁም አዳኝ እንደሆነ በማመን እናከብረዋለን። (ማቴዎስ 20:28፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31) በመሆኑም ክርስቲያን ተብለን እንጠራለን። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) እንዲሁም ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነና ለሥላሴ ትምህርት መሠረት የሚሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ እንደሌለ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውቀናል።—ዮሐንስ 14:28

  4.   የአምላክ መንግሥት። የአምላክ መንግሥት እውን የሆነ መስተዳድር እንጂ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለ ነገር አይደለም። ይህ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚተካ ሲሆን አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስደው በቅርቡ ነው፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚጠቁሙት የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:3-14

     ኢየሱስ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ነው። መግዛት የጀመረው በ1914 ነው።—ራእይ 11:15

  5.   መዳን። ሰዎች ከኃጢአትና ከሞት መዳን የሚችሉት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ የሐዋርያት ሥራ 4:12) አንድ ሰው ከዚህ መሥዋዕት ጥቅም ማግኘት ከፈለገ በኢየሱስ ማመን ብቻ ሳይሆን አኗኗሩን መለወጥና መጠመቅ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 3:16፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19, 20) አንድ ሰው የሚያደርገው ነገር እምነቱ ሕያው መሆን አለመሆኑን ያሳያል። (ያዕቆብ 2:24, 26) ይሁንና መዳን በሥራ ሳይሆን ‘በአምላክ ጸጋ’ የሚገኝ ነገር ነው።—ገላትያ 2:16, 21

  6.   ሰማይ። ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ታማኝ መላእክቱ የሚኖሩት በመንፈሳዊው ዓለም ማለትም በሰማይ ነው። b (መዝሙር 103:19-21፤ የሐዋርያት ሥራ 7:55) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ማለትም 144,000 ሰዎች ከሞት ተነስተው በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ።—ዳንኤል 7:27፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3

  7.   ምድር። አምላክ ምድርን የፈጠረው ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ነው። (መዝሙር 104:5፤ 115:16፤ መክብብ 1:4) አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርካቸዋል።—መዝሙር 37:11, 34

  8.   ክፋትና መከራ። ክፋትና መከራ የጀመሩት ከአምላክ መላእክት አንዱ በማመፁ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ይህ መልአክ ካመፀ በኋላ “ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ” ተብሎ መጠራት የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት በዓመፅ ድርጊቱ እንዲተባበሩት አሳምኗቸዋል፤ ይህ ደግሞ በዘሮቻቸው ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ሮም 5:12) ሰይጣን ላነሳው አከራካሪ ጉዳይ መልስ ለመስጠት አምላክ በምድር ላይ ክፋትና መከራ እንዲኖር ፈቅዷል፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች ለዘላለም እንዲቀጥሉ አይፈቅድም።

  9.   ሞት። ሰዎች ሲሞቱ ከሕልውና ውጪ ይሆናሉ። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10) በእሳታማ ሲኦል አይሠቃዩም።

     አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት እንዲነሱ ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይሁንና ከሞት ከተነሱ በኋላ የአምላክን መንገድ ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ለዘላለም ይጠፋሉ፤ የትንሣኤ ተስፋም አይኖራቸውም።—ራእይ 20:14, 15

  10.   ቤተሰብ። አምላክ የጋብቻ ዝግጅትን ያስጀመረው አንድን ወንድና ሴት በማጣመር ሲሆን እኛም ይህን በጥብቅ እንከተላለን፤ ለፍቺ ምክንያት የሚሆነው የፆታ ብልግና ብቻ እንደሆነ እናምናለን። (ማቴዎስ 19:4-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች የቤተሰብ ሕይወት ስኬታማ እንዲሆን እንደሚረዱ እናምናለን።—ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:1

  11.   አምልኳችን። መስቀልን ወይም ሌሎች ምስሎችን ለአምልኮ አንጠቀምም። (ዘዳግም 4:15-19፤ 1 ዮሐንስ 5:21) በአምልኳችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምንሰጣቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  12.   ድርጅታችን። በጉባኤዎች የተደራጀን ሲሆን እያንዳንዱን ጉባኤ በበላይነት የሚከታተለው የሽማግሌዎች አካል ነው። ሆኖም ሽማግሌዎች የቀሳውስት ቡድን አይደሉም፤ እንዲሁም ደሞዝ አይከፈላቸውም። (ማቴዎስ 10:8፤ 23:8) አስራት አንጠይቅም፤ በስብሰባዎቻችን ላይም ገንዘብ አይሰበሰብም። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ለምናደርጋቸው ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው ስማቸው የማይገለጽ ለጋሾች ከሚያደርጉት መዋጮ ነው።

     በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግለው የበላይ አካል በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አመራር ይሰጣል፤ የበላይ አካሉ አባላት ጥቂት ቁጥር ያላቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች ናቸው።—ማቴዎስ 24:45

  13.   አንድነታችን። እምነታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ አድርጎናል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) በተጨማሪም በመካከላችን በኑሮ ደረጃ፣ በጎሣ፣ በዘር ወይም በመደብ ክፍፍል እንዳይኖር ጥረት እናደርጋለን። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ያዕቆብ 2:4) አንድነት አለን ሲባል የግል ምርጫና አመለካከት የለንም ማለት አይደለም። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ያደርጋል።—ሮም 14:1-4፤ ዕብራውያን 5:14

  14.   ምግባራችን። በምናደርገው ነገር ሁሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ዮሐንስ 13:34, 35) ደም እንደ መውሰድ ካሉ አምላክን ከሚያሳዝኑ ድርጊቶች እንርቃለን። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ገላትያ 5:19-21) ከሰዎች ጋር በሰላም የምንኖር ሲሆን በጦርነትም አንካፈልም። (ማቴዎስ 5:9፤ ኢሳይያስ 2:4) የምንኖርበትን አገር መንግሥት የምናከብር ሲሆን ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የዚያን አገር ሕጎች እንታዘዛለን።—ማቴዎስ 22:21፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29

  15.   ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። እንዲሁም ክርስቲያኖች “የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:39፤ ዮሐንስ 17:16) በመሆኑም ‘ለሁሉም ሰዎች መልካም ብናደርግም’ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ነን፤ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ኅብረት ከመፍጠርም እንርቃለን። (ገላትያ 6:10፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ሌሎች የሚያደርጉትን ውሳኔ እናከብራለን።—ሮም 14:12

 ከይሖዋ ምሥክሮች እምነት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ነገሮችን ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ በድረ ገጻችን ላይ የሚገኘውን መረጃ ማንበብከቅርንጫፍ ቢሮዎቻችን መረጃ መጠየቅበአቅራቢያህ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ መገኘት ወይም በአካባቢህ ያለን አንድ የይሖዋ ምሥክር ማነጋገር ትችላለህ

a ትሩዝ ኢን ትራንስሌሽን የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 165 ተመልከት።

b ክፉ መላእክት ከሰማይ ቢባረሩም አሁንም የሚኖሩት በመንፈሳዊ ዓለም ነው።—ራእይ 12:7-9